የኔታ እንደሥራቸው አግማሴን በሚመለከት በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ በአውሮፓ ሀገረ ስብከት በጀርመን ሀገር በምንገኝ ማህበረ ካህናት የወጣ የጋራ የአቋም መግለጫ

blog-img

09, Juni, 2018Posted by :admin(0)Comments

የኔታ እንደሥራቸው አግማሴን በሚመለከት በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ በአውሮፓ ሀገረ ስብከት በጀርመን ሀገር በምንገኝ ማህበረ ካህናት የወጣ የጋራ የአቋም መግለጫ

የአቋም መግለጫውን ለማንበብ ይህንን ይጫኑ

 

አራት ዐይናው የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ የኔታ እንደሥራቸው አግማሴ ፈጣሪ የሰጣቸውን  ነጻነት ተገፈው፣ እንደ ሰው የመንቀሳቀስ መብታችውን ተነጥቀው፣በድንገት ከመንገድ ላይ ታፍሰው፣እንደ አውሬ በበርሀ ጉድጓድ በማይታወቅ እስር ቤት ውስጥ እጅግ ለአእምሮ በሚከብድ ሁኔታ እየተሰቃዩ ይገኛሉ:: የእስር ቤቱንም ስቃይ በውስጡ የነበሩና ያለፉ ወንድሞችና እህቶች ያሳለፉትን ግፍና ሰቆቃ ለዓለም ሕብረተሰብ ሲገልጡና ሲያጋልጡ ሰምተናል:: ምስጋና ለፈጣሪ ይድረሰውና በዚህ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ግን የሞትና የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው ሳይቀር ከእስራት ነጻ እንዲሆኑ በመደረጉ ደስታችን ወሰን የለውም:: ይህ የተቀደሰ ጅምርም አስታዋሽ የሌላቸውንም እንደሚጨምርና ከእስር ነጻ እንደሚወጡ ተስፋ እናደርጋለን::

እኛ በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ በአውሮፓ ሀገረ ስብከት በጀርመን ሀገር የምንገኝ ማህበረ ካህናት በፍራንክፈርት ከተማ በሚገኘው በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስትያን ጽ/ቤት ተሰብስበን ለ24 ዓመታት ያለ ሕግ አግባብ በሕገ ወጥ መንገድ ከቤተ ሰብና ከቤተ ክርስቲያን ተለይተው ስለታሰሩት የዘመናችን ሊቅ ስለ ሆኑት የኔታ እንደሥራቸው አግማሴን በሚመለከት የወጣ የጋራ የማህበረ ካህናት የአቋም መግለጫ ፣

  1. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ ዐይን ብሌን ከሚታዩት ሊቃውንት ውስጥ ፈርጥ የሆኑት የተክሌ አቋቋም ምስክር የድጓ መምህርና አዲስ ዜማ ደራሲ፣ የቅዳሴና የቅኔ ተጠያቂ መምህር የሆኑት የዘመናችን ያሬድና ተክሌ የሚል ስም የተሰጣቸው አራት ዐይናው ሊቅ አንደስራቸው አግማሴ በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስራት አንዲፈቱ እንጠይቃለን።
  2. ሊቁ እንደሥራቸው አግማሴ በሚኖሩበት በጎንደር ከተማ የዕለት ተግባራቸውን ሲያከናዉኑ ውለው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ በመንገድ ላይ ድንገት ታፍነው ከተወሰዱበት ዕለት ጀምሮ ከቤተ ክርስቲያንና ከቤተሰብ ተሰውረው ምክንያቱ በማይታወቅ ሁኔታ እስካሁን ድረስ የተፈጸመባቸውን ኢሰብአዊ ድርጊት አጥብቀን እንቃወማለን።
  3. ለ24 ዓመታት ሊቁን እንደሥራቸው አግማሴን ከቤተሰብ ለይቶ ማስቃየት ወደር የሌለው ኢሰብአዊነት ከመሆኑም በላይ የቤተ ክርስቲያኗንም ትልቅ የትምህርት ማዕከል ለማምከን ታስቦ የተሰራው ሃላፊነት የጎደለውና ጥላቻን መሰረት ያደረገው ተግባር ቆሞ ሊቁ እንደሥራቸው አግማሴ አንዲፈቱ ድምጻችን ከፍ አድርገን እናሰማለን::
  4. ከልጅነት እስከ እውቀት ከተማሪነት እስከ መምህርነት ከመምህርነት እስከ ሊቅነት አስተምራ ያሳደገቻቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከእስር ተፈተው ገደብ የሌለውን ምጡቅ እውቀታቸውን ለተትኪው ትውልድ እንዲተላለፍ ካላት ፍላጎት አንጻር ሊቁ እንደሥራቸው አግማሴ ተፈተው ከቤተሰባቸው እስከሚቀላቀሉ ድረስ የይፈቱ ጥያቄያችን የሚቀጥል መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን ::
  5. ሊቁ እንደሥራቸው አግማሴ ከጎንደር ጀምሮ አሁን እስካሉበት ትግራይ በሚገኝ የጨለማ እስር ቤት ለመታሰራቸው ምንም ሳያደርጉ በማንነት ጥላቻ ላይ በተመሰረተ ምክንያት የደረሰባቸው ግፍና መከራ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እንደ ወረደ መዓት እናየዋለን:: ይህ አሳፋሪና ኢሰብአዊ ታሪክ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ጥሎ ያለፈውን አሻራ ግን በታሪክ ሳይቀር ቤተ ክርስቲያን ወደፊት የምትዘነጋው አለመሆኑን ሊታወቅ ይገባል::
  6. ሊቁ እንደሥራቸው አግማሴ ከልጅነት ጀምሮ የሚያውቋቸው ሰዎች ሁሉ እንደሚመሰክሩላቸው ሰውን አክባሪ ሁሉንም ሰው አፍቃሪ ሙያቸውን አክባሪና ለሁሉም ሰው በችግሩ ደራሽ መልካም ሥነ ምግባር የተላበሱ ለቤተሰባቸው ልዩ ፍቅር ያላቸው እንከን የለሽ ሰብዕና ያላቸው እንደሆኑ ሁሉም የሚያውቀው ሀቅ ነው ከጥላቻና ከፖለቲካ የጸዱ የቤተ ክርስትያን የስስት አባት ሲሆኑ የመታሰራቸው ምክንያት ለብዙዎቹ ያልተፈታ እንቆቅልሽ እንደሆነ ለሁሉም ግልጽ ነው:: ስለዚህ ሊቁ እንደሥራቸው አግማሴ ተፈተው ቀሪ ጊዚያቸውን እናት ቤተ ክርስቲያንን በሙያቸው እንዲያገለግሉ፣ ሙያቸውን ለተተኪው ትውልድ እንዲያስተላልፉ፣ ለ24 ዓመታት በሀዘን የተጎዳው ቤተሰብ ከሀዘኑ እንዲረጋጋ የ71 ዓመቱ አዛውንት ሊቁ እንደሥራቸው እንዲፈቱ ጥያቂያችን እናቀርባለን::

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ዓለምን ሁሉ ይባርክልን

Leave Comments