የብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የበዓለ ልደት መልእክት

blog-img

06, Januar, 2019Posted by :admin(0)Comments

እንኳን ለጌታችንና ለመድኀኒታች ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ እላለሁ። በዓሉም የሰላምና የደስታ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።

ልደተ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ተለይቶ የነበረው ሰው ከእግዚአብሔር  ጋር የታረቀበት፣ ሕዝብና አሕዛብ አንድ የሆኑበትና ሰማያውያን መላእክትና ምድራውያን ደቂቀ አዳም በአንድ ላይ ሆነው 

  “ ስብሐት ለእግዚአብሔር በሠማያት ወሰላም በምድር ለዕጓለእመሕያው ስምረቱ  ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ “  


ሉቃ ፪:፲፬ 

እያሉ የሰላምን መዝሙር በአንድ ላይ ሆነው የዘመሩበት በዓል  ነው።


በተለይ የዚህ ዓመት የልደት በዓል እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ በመሆኑ  ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ በሁለት ሲኖዶስ ተለይታ የቆየችው እናት ቤተ ክርስቲያንችን ሲኖዶሳዊ አንድነቷ ተመልሶና ተለያይተን የነበርነው የቤተ ክርስቲያን ልጆች በአንድ ላይ መዘመር ፣መጸለይ ፣ ማመስገን፣ ማገልገልና መገልገል በጀመርንበት ወቅት የሚከበር በዓል በመሆኑ  የተለየ ነው።
  ምንም እንኳን በዓሉ የፍቅርና የአንድነት  ፣የደስታና የሰላም ፣የይቅርና የርሕራኄ  በዓል መሆኑ ቢታወቅም ዛሬም ሰዎች  ራሳቸው በሚፈጥሯቸው የልዩነት ግንቦችና ለልዩነት ምክንያት ሊሆኑ በማይገባቸው ምክንያቶች  ጎራ ለይተው እርስ በእርሳቸው በክፉ የሚፈላለጉበት ወቅት በመሆኑ ሁላችንም በልደቱ ብርሃን ይህን የልዩነት ጨለማ በማሶገድ ፍጹም የሆነ ክርስቲያናዊ አንድነትን እውን የምናደርግበት በዓል ሊሆን  ይገባል።
በልደቱ አማካኝነት የተማርነው ትምህርት አንድነትን፣ እርቅን፣ሰላምን፣ስምምነትን፣፣ኅብረትንና ፍቅርን በመሆኑና በዚሁ ዕለት በሰማያውያንና በምድራውያን ፍጥረታት በጋራ የተዘመረውም መዝሙር የሰላም መዝሙር ስለሆነ ሁላችንም በበዓሉ ላይ ይህን ትምህርት ስንሰማና የሰላም መዝሙር  ስንዘምር እውነተኛ  የፍቅርና የሰላም ሰዎች መሆናችንን በተግባር እያሳየን ሊሆን ይገባል።

በተጨማሪም  በዓሉን ስናክብር በተለያዩ ምክንያቶች የተለያየን ካለን አንድ ሆነን፣ የተጣላን ታርቀን ፣የተራራቅን ተቀራርበንና ችግሮች ቢኖሩም እንኳን ክርስቲያናዊ በሆነና በሰለጠነ  መንገድ በውይይት እየፈታን  ቢሆን ከእግዚአብሔር በረከትን እንቀበላለን።
የክርስቶስ ልደት ለሁላችንም  የደስታ በዓል መሆኑንመልአኩ ጌታ በተወለደበት አካባቢ ከብቶቻቸውን ይጠብቁ ለነበሩ እረኞች ባሰማቸው የምሥራች ቃል :

„እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፡ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” 

ሉቃ. ፪፡፲-፲፪

ሲል እንደተናገረው ሁላችንም ፍጹም በሆነ መንፈሳዊ ደስታ ልናክብረው ይገባናል

ይህ ዓመት በአንድ በኩል የቤተ ክርስቲያናችንን የአንድነት ዜናና ሌሎችንም በጎ ነገሮችም የሰማንበትና ያየንበት በመሆኑ እጅግ ደስ የተሰኘንበት ቢሆንም  በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ደግሞ የሚሰሙና የሚታዩ አሳዛኝ ክስተቶች አሉና እግዚአብሔር ለሀገራችን ፍጹም ሰላምን ለሕዝቡም አንድነትንና ፍቅርን እንዲሰጥልን አብዝተን ልንጸልይ ይገባናል።


መልካም በዓለ ልደት

ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የጀርመን እና አካባቢው ሃገረ ስብከት ጳጳስ

Schlagwörter: ,

Leave Comments